ፕሬስ ሪሊዝ

image description
- In የከተማ ግብርና ልማት ዘርፍ    0

ፕሬስ ሪሊዝ

ፕሬስ ሪሊዝ


የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ የማቋቋምና የማልማት፣ አርሶ አደሮች ከከተማዋ ልማት ጋር አብረው እንዲለሙ የማድረግ፣ የከተማ ግብርናን የማስፋፋትና የማጠናከር፣ የግብርና ምርትና አገልግሎት ጥራት፣ ኋይጅን እና ደህንነት ተጠብቆ ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥራዎችን ይሰራል፡፡


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት ባወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 መሰረት ኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል በመንግስት፣ በማህበራት እና በግል ቄራ ድርጅቶች የእርድ እንስሳትና የሥጋ ምርመራ አገልግሎት ይሰጣል፤ ይቆጣጠራል፤ ሕገ-ወጥ የእንስሳት እርድና በሕገወጥ መንገድ የታረዱ እንሰሳት ሥጋ ዝውውርን ይቆጣጠራል፤ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል እንዲወሰድም ያደርጋል፡፡


በከተማችን አዲስ አበባ በበርካታ ቦታዎች ላይ ህገ-ወጥ የሆነ የእንስሳት እርድና ሥጋ ዝውውር በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይህ አስነዋሪ ተግባር ደግሞ ከእንስሳት ወደ ሰው ለሚተላለፉ ሥጋ ወለድ በሽታዎች መስፋፋት ምክንያት በመሆኑ ብዙዎች ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡


እጅግ በጣም ብዙ ከሰው ወደ እንስሳትና ከእንስሳት ወደ ሰው ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች (zoonoses) አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ወደ ሰው የሚተላለፉት የእንስሳት ውጤት በሆኑት በሥጋ፣ በሥጋ ውጤቶችና በሌሎች የእንስሳት ተዋጽዖ ምክንት ነው፡፡


ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ሥጋ ወለድ በሽታዎች ዋና ዋና ምክንያቶች የተለያዩ ባክተሪያዎች፣ ሞልድ /ፈንገስ/፣ ቫይረሶች፣ የተለያዩ ትላትሎችና መርዛማ ኬሚካሎች ናቸው፡፡
በበሽታ አምጪ ተዋስያን (microorganism) በተበከለ ሥጋ ሳቢያ የሚከሰቱ በሽታዎች ቀላል የማይባሉ ናቸው፡፡ በአንጀት ውስጥ በመራባት በሽታን ሊፈጥሩ የሚችሉ ባክቴሪያዎች፣ ለምሳሌ ሳልሞኔሎሲስን ማንሳት ይቻላል፡፡


ሌላው በጥገኛ ተዋህስያን ሳቢያ የሚከሰቱ ሥጋ ወለድ በሽታዎች የከብት ኮሶ ትል (Cysticercus vovis)፣ የአሳማ ኮሶ ትል (Cysticercus cellullosae)፣ የአሳ ኮሶ ትል (Diphyllobothrim latum)፣ የውሻ ኮሶ ትል)፣ (Echinococcous Granullosis or Hydatidosis Disease) እንደነዚህ ያሉት በተፈጥሯቸው ከሰው ወደ እንስሳትና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው፡፡


የእርድ እንስሳት ንጽህናቸው ባልተጠበቀ የቆሸሹ ቁሳቁሶች፣ ስፍራዎች፣ በቆሸሹ እጆች፣ ልብሶች፣ ከሚታረደው እንስሳ ቆዳና ሌጦ፣ ፈርስ ወዘተ.. ጋር በሚደረገው ንክኪ፣ ሥጋውን ለመያዝ፣ ለማጓገዝ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የቆሸሹ መያዥያዎች፣ መስፈርት፣ ያልጠበቁ ማጓጓዣዎች በሚተላለፉ ተዋህሲያንና ከታመሙ ከብቶች በሚወጣው ቆሻሻ የተበከለ ሥጋን መመገብ ለጤና ጠንቅ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚኖረውና የሚነቀሳቀሰው ህዝብ በሚሊዮን የሚቆጠር ነው፡፡ በተጨማሪም አዲስ አበባ በየቀኑ በርካታ ህዝብ የሚገባባትና የሚወጣባት፣ የሀገሪቱ ርዕሰ መዲና፣ የአፍሪካ ህብረትና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ መቀመጫ ከተማ ነች፡፡


ከዚህ አንጻር ሥጋ ተጠቃሚ ከሆነው ህብረተሰብ አብዛኛው ሥጋን በጥሬውና በተለያየ መልክ አዘውትሮ የሚመገብ ነው፡፡ በመሆኑም የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ ይቻል ዘንድ ለህብረተሰቡ የሚቀርበው ሥጋና የሥጋ ውጤቶች በህጋዊ ቄራ ድርጅቶች  የሥጋ ምርመራ ሂደትን አልፎ ጤናማነቱ ተረጋግጦና ኃይጅኑ ተጠብቆ  የሚቀርብ መሆን አለበት፡፡ 


ስለሆነም ህገ-ወጥ የእንስሳት እርድና ህገ-ወጥ ሥጋ ዝውውር መቆጣጠር በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሥጋ ወለድ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር የአምራቹን ህብረተሰ ጤና መጠበቅ ምርታና ምርታማነትን ማሳደግ በመሆኑ መጭውን የ2017 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በህገ-ወጥ መንገድ ታርደው ለህብረተሰቡ ከሚቀርቡ ጤናማነታቸው ካልተረጋገጠ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች ማህበረሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡


በመሆኑም በእጅጉ ተንሰራፍቶ ዘርፈ-ብዙ ችግር እያስከተለ የሚገኘውን ህገ-ወጥ የእንስሳት እርድና ሥጋ ዝውውር መቆጣጠር፣ መከላከልና የተግባሩ ፈፃሚዎችን ለህግ እንዲገዙ ማድረግ ተገቢነት ያለው በመሆኑ የሚመለከተን ተቋማት ተቀናጅተው በመስራት መቀነስ ብሎም ማስቀረት የሚያስችል አሰራርን እንድንፈጥር አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡


ሌላው በህገ-ወጥ መንገድ እርድ ሲፈጽሙ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሥጋ ሲያዘዋውሩ የተመለከተ ማህበረሰብ ጥፋተኞቹ በህግ እንዲጠየቁ ጥቆማዎችን እንድትሰጡ እናሳስባለን፡፡

መጭው የትንሣኤ በዓል የሰላምና የብልጽግና እንዲሆን እንመኛለን፡፡ በድጋሚ መልካም በዓል፡፡
                                          
እግዚአብሔር ኢትዮጲያንና ህዝቧን ይጠብቅ


                                                  ሚያዝያ 07/08/ 2017 ዓ.ም
                                                 አዲስ አበባ፣ ኢትዮጲያ


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments