ለትንሣኤ በዓል ከብር 90, 000 እስከ ብር 100,000 የሚሸጥ ሰንጋ አዘጋጅተናል፡፡
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 08 ቀን 2017 ዓ.ም
የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማእከል ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንስካሁን በዳልጋ ከብት ማድለብ ዘርፍ በማህበር ተደራጅተው የተሰማሩ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች አምስት ዙር በተሳካ መልኩ የዳልጋ ከብቶችን በማድለብ ለገበያ አቅርበዋል፡፡
የማህበሩ አባል የሆኑት አቶ አዲሱ ጫላ ማህበራቱ የተፈጠረላቸውን የገበያ ትስስር በመጠቀም ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ 83 የደለቡ ከብቶች ያሉ ሲሆን 72ቱ ለገበያ ዝግጁ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ታቦሩ አበበ በወተት ከብት እርባታ ላይ የተሰማሩ የማህበር አባል ሲሆኑ ለመጭው የትንሣኤ በዓል ከሌላው ጊዜ በተለየ የወተት ምርት ለገበያ ያቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም በቀን እስከ 530 ሊትር ወተት ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ የሥጋ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ስሜነህ አማረ ማእከሉ ከተመሰረተ ጀምሮ ለ5ኛ ዙር በ2017 በጀት ዓመት ወደ 300 የዳልጋ ከብቶች በማድለብ ለገበያ ያቀረበ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አያይዘውም ለትንሳኤ በዓል ዋጋቸው ከብር 90, 000 እስከ ብር 100,000 የሚሸጡ 72 የዳልጋ ከብቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከዋጋ አንፃር ተመጣጣኝ፣ የጤና ሁኔታ በባለሙያ ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩ፣ አመጋገባቸው ሳይንሱን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በም/ኮሚሽነር ማዕረግ የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማእከል ኃላፊ የሆኑት አቶ አሌክስ ደመቀ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ለትንሣኤ በዓል ዝግጅት እንደተደረገ እና ምርቶቹም በማዕከሉ የመሸጫ ሱቆች እና አቧሬ አደባባ አካባቢ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በቀን 530 ሊትር ወተት በሊትር በብር 75 እየቀረበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments