
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ!።
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም
@✨✨✨
የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን 500 ለሚሆኑ ዜጎች የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል አቦ አካባቢ የማዕድ ማጋራት አካሂዷል።
በመርሃ-ግብሩ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዮ ሽጉጤ፣ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን አበበ፣ ም/ኮሚሽነሮች ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ፣ አቶ መለስ አንሼቦ፣ ፀጋ ለማ (ዶ/ር)፣ ዳይሬክቶሬቶች፣ ባለሙያዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የእለቱ ምገባ የሚደረግላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዮ ሽጉጤ ዘመናትን የተሻገሩ የአንድነታችን ምሰሶ የሆኑ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የመተጋገዝ እሴቶች ጎልተው መውጣት እንደሚገባቸው ገልፀዋል።
አክለውም ከለውጡ ወዲህ በዓላትን በአብሮነት የማሳለፍ እንዲሁም አቅመ ደካሞችን የመጠየቅ ልምድና እሴቶች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ከሰው ተኮር ስራዎች አንዱ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ወገኖች ጋር አብሮ ዐበይት በዓላትን በማሳለፍ አብሮነትን በዘላቂነት ማበልፀግ መሆኑን ገልፀዋል።
የፕሮግራሙ ተሳታፊ የነበሩት የኮሚሽኑ አመራሮችም ለውጡን ተከትሎ የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴቶቻችን እየዳበሩ የመጡ ሲሆን ለዚህ ደግሞ መንግስት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን ለመመገብ ያቋቋመው የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
በዓልን በዚህ መልኩ ከአቅመ ደካሞችና ከተቸገሩት ጋር ማሳለፍ ልብን የሚሞላ ለህሌናም ትልቅ እርካታ በመሆኑ ይህን በጎ ተግባር መደገፍ የሁሉም ወገኖች የቤት ሥራ መሆን አለበት ብለዋል።
የማዕድ ማጋራት የተደረገላቸው ወገኖችም ስለተደረገላቸው ነገር ከልብ አመስግነዋል፤ መርቀዋል።
ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዮ ሽጉጤ ሀገራችን ኢትዮጲያ በመደጋገፍ ላይ የተመሰረቱ በርካታ መልካም ማህበራዊ እሴቶች ያሏት ሀገር ስትሆን መንግስት እነዚህ እሴቶች የበለጠ ሰፍተውና አድገው እንዲገኙ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments