
የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይትና የሥራ ትስስር ስምምነት የፊርማ ሥነ-ስርዓት ተደርጓል።
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም
በመድረኩም የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ፣ ም/ኮሚሽነሮች ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻና አቶ መለሰ አንሼቦ፣ የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ሀብተየስ ዲሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ሥራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አሰፋ፣ የክፍለ ከተማ የዘርፉ የጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የሙሌ መኖ ማቀነባባሪያ ድርጅት የኤም.ኤስ.ኤ ንግድ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ፣ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት አመራሮች እና የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማ የእንስሳት መኖ አቅርቦትን በተመለከተ ለእንስሳት አርቢዎች መኖን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል ከሚመለከታቸው በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር የጋራ የሆነ አሰራር መፍጠር ነው፡፡
ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ ከመኖ ዋጋ መጨመር ጋር በተያያዘ አርቢዎች ሰፊ ጥያቄ ያላቸው መሆኑን አንስተው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከእናንተ ጋር የጋራ የሆነ አሰራር መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ይህ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
አያይዘውም ከኤም.ኤስ.ኤ ንግድ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ጋር በተደረገ ስምምነት ኮሚሽኑ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ መኖ የሚቀርብበትን አሰራር ያስቀመጠ በመሆኑ በእናንተ በኩል የድርሻችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡
ሌላው የእንስሳት ግብዓትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት አመቻች ቡድን መሪ አቶ ሃይሉ ቀዲዳ ለውይይት የሚሆነውን የመወያያ ሰነድ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ አካላትም በየበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ተግተው የሚሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነሮችም ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት የአርቢዎች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ግብርና በከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ እንዲወጣ በጋራ መስራት የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments