769 የጋራ መኖሪያ ንግድ ቤቶች ለኮሚሽናችን በሽያጭ ተላልፈዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም
የአርሶ አደር ማቋቋምና ልማት ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ አርሶ አደሮች ከከተማዋ ልማት ጋር አብረው እንዲለሙ የለውጡ መንግስት በርካታ ሰው ተኮር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
አክለውም በልማት ምክንያት ከይዞታቸው ያለበቂ ቅድመ ዝግጅት የተነሱ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን ለአብነትም የመስሪያ ቦታ ማመቻቸት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የአርሶ አደር ማቋቋምና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረጋሣ ባይሣ ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በኩል ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ የንግድ ቤት እንዲሰጣቸው ውሳኔ ያሳለፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ከ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም ከተገነቡት የጋራ ንግድ ቤቶች ውስጥ በሽያጭ 769 (ሰባት መቶ ስልሳ ዘጠኝ) የንግድ ቤቶች ካርታ ተዘጋጅቶላቸው ለተጠቃሚዎቹ እንዲተላለፉ በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በኩል አቅጣጫ እንዲሰጥበት አድርገናል ብለዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የክ/ከተሞች መሬት ልማት እና አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ስም ካርታ እንዲያዘጋጅ እና በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በኩል ደግሞ ፋይል እንዲያደራጁላቸው አቅጣጫ መቀመጡን የወረደው ደብዳቤ ይገልፃል፡፡
ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ የተጠቀሰውን ተግባር ለመፈፀም ሌብነትና ብልሹ አሰራር ፈታኝ ስለሚሆን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት እንደሚገባ አጽህኖት በመስጠት አንስተዋል፡፡
በተያያዘም የክፍለ ከተማና የወረዳ የዘርፉ ጽ/ቤቶች በወረደው መስፈርት መሰረት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮቹን መረጃ አደራጅተውና ገምግመው በአስቼኳይ መላክ እንዲችሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments