ሙስና በማህበረሰቡ ቀደምት ብሂሎች ውግዝ ነው።

image description
- In የከተማ ግብርና ልማት ዘርፍ    0

ሙስና በማህበረሰቡ ቀደምት ብሂሎች ውግዝ ነው።

ሙስና በማህበረሰቡ ቀደምት ብሂሎች ውግዝ ነው።


አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም


የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በአስቼኳይ ጊዜ የሙስና መከላከል ጽንሰ-ሃሳብ፣ መገለጫዎች፣ የሚያስከትለው ጉዳትና መከላከያ መንገዶቹ ላይ ከአመራሮችና ጠቅላላ ሰራተኞች ጋር የፓናል ውይይት አኳሂዷል፡፡

ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ ሙስና ዘርፈ ብዙ መገለጫ ያለው ኢ-ሞራላዊ ተግባር በመሆኑ ግለሰብን፣ ማህበረሰብን፣ ተቋምን ብሎም ሀገርን በእጅጉ የሚጎዳ ስለሆነ ሁላችንም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በመፀየፍ፣ በመታገል እና በመከላከል የበኩላችንን ሚና መወጣት ይገባል ብለዋል፡፡

በአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት “ሙስና” መቅሰፍት ነው። ጥፉት፣ ብልሹ፣ ግም፣ መበስበስ፤ መከራ”...  እና በመሰል ነውርን በሚገልጡ ቃላት ይፈቱታል። ሙስና በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ኃጢያት፣ በዓለማዊ ሕጎች ወንጀል የሆነ በማህበረሰቡ ቀደምት ብሂሎች ውግዝ ነው።

ኦክስፎርድ መዝገበቃላትም ሙስናን (Corruption) ከአለመታመን/እምነትን ከማጉደል፣ ምግባረ ቢስነት፣ ጉበኝነት እና በመሰል ቃላት ይገልፀዋል። ከዝቅጠትና ከመቆርቆዝ ጋር ያቆራኘዋል።

በመሆኑም ሙስና የማህበረሰቡን የሞራል፣ የሕግና ፍትሕ እሴቶች ይንዳል፤ የፖለቲካ ብክለት መገለጫ ነው፤ የነባር ግብረ ገባዊ እሴቶች መናድ ማሳያ ነው፤ ለማኅበረሰብ ሕልውና አደጋ ነው፡፡ 

ሌላው ሙስና ምቾት፣ ቅምጥልነትና ራስ ወዳድነት መንፈስ የተጠናወተው እኩይ ምግባር መላበስ ነው። በጥቂቶች ብዙሃኑን የሚበክል ድርጊት ነው። እናም ኢ-ፍትሐዊነት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ አድልዎ እና የሞራል ዝቅጠት እንዲለመድ ያደርጋል።
እንደ ፓናል ውይይት ሰነድ አቅራቢዎቹ አገላለጽ ሙስና እጅግ በርካታ መገለጫዎች ያሉትና ኢ-ሥነ-ምግባራዊ ድርጊት በመሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊያወግዘውና በጽኑ ሊከላከለው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ጥናቶች ሙስናን በተለያዩ ደረጃዎችና መልኮች ይገልጹታል። መጠነ ሰፊ ሙስና፣ አነስተኛ ሙስና፣ ፖለቲካዊ መስና እና ስልታዊ ሙስና በሚል ይመደባሉ።

ሙስና ድህነትን ያባበሳል፤ ሰብዓዊ መብትና ክብርን ይገፋል፤ የዳበረ ባህልን ይሸረሽራል፤ ዕድገትን ይጎትታል፤ ግጭት ይቀሰቅሳል፤ የመንግስትን ቅቡልነት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ይፈታተናል።

መልኩ ምንም ይሁን ምን ሙስና ጠንክሮ መስራትን የሚኮንን፣ ሳይሰሩ መብንላትን የሚያጀግን፣ የአጋርነትን ሞራል የሚሰብር፣ ሀገርን ለደህንነት ስጋት አደጋ የሚጥል፣ ኢንቨስትመንትን የሚያቀጭጭ፣ መረጋጋትን የሚፈትን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ዘላቂ ልማትን የሚገታ ነው።

የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርጋ ጢጣ ሙስና በተለያየ መልኩ ሊተገበር የሚችል ብልሹ ተግባር በመሆኑ እንደ ኮሚሽን በተለይም ለሌብነትና ብልሹ አሰራር ተጋለጭ ናቸው ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments