ግብርና የኢኮኖሚያችን መሰረት ነው፡፡

image description
- In የከተማ ግብርና ልማት ዘርፍ    0

ግብርና የኢኮኖሚያችን መሰረት ነው፡፡

ዜና ትንታኔ

ግብርና የኢኮኖሚያችን መሰረት ነው፡፡


አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም



ግብርና ለአብዛኛው የዓለም ህዝብ ባህል እና የኢኮኖሚ ምንጭ ነው፡፡ አሁን ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ብዙዎች ከዕለት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ ማምረት እንዲችሉ አስችሏል፡፡ 
ግብርና የኢትዮጵያዊያን የዕለት ጉርስ መገኛ፣ የገቢ ምንጭ፣ የአገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት፣ ለአብዛኛው የአገሪቷ ህዝብ የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ እድገት ምጣኔ ቀዳሚ ደረጃ ላይ የተቀመጠና የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ነው፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ገጠር ላይ ብቻ ይታወቅ የነበረው ግብርና ዛሬ በመላው ዓለም በከተሞች ደረጃ የከተማ ግብርና ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ የገቢ ምንጭ ሆኗል፤ ብዙዎች የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የተወሰኑ የዓለማችንን ከተሞች ለአብነት ብንመለከት የሲንጋፖር ከተማ 10 በመቶ ያህሉን የምግብ ፍጆታዋን በከተማ ግብርና ለመሸፈን በቅታለች፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ከሚያስፈልጋት የግብርና ምርት ውስጥ 30 በመቶውን በራሷ ለመሸፈን በመስራት ላይም ትገኛለች፡፡
የሚችጋኗ ዲትሮይት ከተማ ነዋሪዎቿ በከተማ ግብርና የቤት ውስጥ ፍጆታቸውን ከመሸፈን አልፈው ምርቶቻቸውን ለሱፐር ማርኬቶች በማስረከብ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡
ለንደን ከመደበኛው ግብርና 70 በመቶ የውሃ ፍጆታን የሚቆጥብ የምድር ውስጥ የከተማ ግብርና ታከናውናለች፡፡ ምርታማነቱ ደግሞ በእጥፍ ይበልጣል (በመደበኛው የምድር ላይ ግብርና በአንድ ሄክታር መሬት 20 ኩንታል ምርት የሚገኝ ሲሆን በምድር ውስጥ ግብርና በሄክታር 40 ኩንታል ምርት ይገኛል እንደማለት ነው፡፡
ለአብነት ከላይ ያሉትን አነሳን እንጂ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ ኮሎምቢያ፣ ህንድ፣ ኩባ እና ሌሎችም በርካቶች በከተማ ግብርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሀገራት ናቸው፡፡
በአህጉራችን አፍሪካም ስንመለከት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ በፊት የከተማ ግብርና የሚያከናውኑት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ማለትም ስደተኞች፣ ሥራ አጦች፣ የጥበቃ ሰራተኞች እና የቤት እመቤቶች ነበሩ፡፡
ከ1972 በኋላ ግን በርካታ በመካከለኛና በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ከተማ ግብርና ሥራ መግባትና መተግበር እንደጀመሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የከተማ ግብርና ተገባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በጋና አክራ በ1972 በዘመቻ ራስህን መግብ (feed your self-operation) ጋና ዛሬ ለደረሰችበት የከተማ ግብርና ዕድገት ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቶላታል።
በዚህም የመንግስት ባለስልጣናትና ከፍተኛ ባለሙያዎች በወቅቱ በአክራ የተከሰተው ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሁኔታ ወደ ከተማ ግብርና ልማት እንዲገቡ አስገድዷቸዋል፡፡
ሌላዋ የአፍሪካ ሀገር ኬንያ በግብርና ሥራ ለተሰማሩ ዜጎቿ የተለያዩ የብድር አቅርቦት አማራጮችን የምታቀርብ ሲሆን በእንስሳት እርባታ ለተሰማሩ የሚሆን የፋይናንስ አቅርቦት (Livestock Loan)፣ የሥራ ማስኬጃ ብድር (Working Capital Loan)፣ የግብርና ውጤቶችን ለሚያቀነባብሩ (Agro Processors)፣ የሰብል ብድር (Crop Loan) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንደ ሀገር ብሎም በከተማችን አዲስ አበባ የከተማ ግብርና ከመቸውም በላይ እየተስፋፋና እየተጠናከረ የመጣበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የሌማት ትሩፋት የበርካቶችን ጓዳ አንኳኩቶ ገብቶ በማዕድ ላይ የቅንጦት የነበሩ ምግቦች ዛሬ የዕለት ከዕለት ምግብ እንዲሆኑ ለማስቻል ትልቅ የሆነ ማሳያ ሆነዋል፡፡
የሀገራችን ህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሜነት መስፋፋት፣ የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ መምጣት፣ በከተማ ደረጃ የግብርና ምርት አቅርቦት ፍላጎት መጨመር፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ተፅዕኖች እየተባባሱ መምጣት ግብርና በከተማ ውስጥ እንዲተገበር የግድ ብሏል፡፡
በመሆኑም በ2012 በጀት ዓመት 157,502 የከተማ ግብርና ተሳታፊ (ተጠቃሚ) የነበረ ዛሬ በከተማችን አዲስ አበባ 1,028,253 ተሳታፊ (ተጠቃሚ) ደርሷል፡፡
ከምርትም ጋር በተያያዘ በ2011 በጀት ዓመት በእንስሳት እና በእጽዋት ሃብት ልማት 49,310 ቶን ይገኝ የነበረ አመታዊ ጠቅላላ ምርት መጠን በአሁን ሰዓት በ2017 በጀት ዓመት 280,406 ቶን ምርት ማምረት ተችሏል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘም በ2011 በጀት ዓመት ለ1,672 ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት 26,311 ዜጎች በከተማ ግብርና የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments