የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በሌማት ትሩፋት ለሚሰማሩ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ ግብዓቶችን አበረከተ፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በሌማት ትሩፋት ለሚሰማሩ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ ግብዓቶችን አበረከተ፡፡
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19 ቀን 2018 ዓ.ም
አስተዳደሩ ከአሥራ አንዱም ወረዳዎች ለተውጣጡና በሌማት ትሩፋት በዶሮ እርባታ ለሚሠማሩ 135 ቤተሰቦች እንቁላል ጣይ ዶሮዎች፣የዶሮ ኬጆች እና የዶሮ መኖ ያበረከተ ሲሆን፣ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም አሰፋ ባደረጉት ንግግር የክፍለ ከተማው አስተዳደር የከተማ ግብርና እንዲስፋፋና ነዋሪዎች የምግብ ዋስትናቸውንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በሌማት ትሩፋት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
“ዛሬ የግብዓት ድጋፍ የተደረገላችሁ ወገኖቻችን ከዚህ ቀደም በዘርፉ ውጤታማ እንደሆኑ ነዋሪዎች ሁሉ በትጋት በመሥራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታችሁን ማረጋገጥ ይጠበቅባችኋል” ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ተጠቃሚዎቹ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የክፍለ ከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ባሕሩ በበኩላቸው ለተጠቃሚዎቹ በነፍስ ወከፍ 10 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እና እያንዳንዳቸው 50 ዶሮዎችን የሚይዙ 27 የዶሮ ኬጆች እንደተበረከቱላቸው ገልጸው፣ የድጋፉ ዓላማ አዲስ አበባ ከሸማችነት ወደ አምራችነት እንድትሸጋገር በሚደረገው ርብርብ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም ዜጎች በዘርፉ ተደራጅተው በመሥራት የከተማ ግብርና እንቅስቃሴን እንዲያሳድጉ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments