የተረጂነት ቅነሳ ግብረ-ሃይል የ6ቱ ግቦች የ78 ቀን አፈፃፀሙን ገመገመ።
የተረጂነት ቅነሳ ግብረ-ሃይል የ6ቱ ግቦች የ78 ቀን አፈፃፀሙን ገመገመ።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ "በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እምርታ" የስራ እድል እና የተረጂነት ቅነሳ ግብረ-ሃይል የ6ቱ ግቦች የ78 ቀን አፈፃፀሙን ገምግሟል።
በዕለቱም በቀጣይ ጊዜ በትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በ3 ወር ለማከናወን ከታቀዱ የስራ እድልና የሌማት ትሩፋት ተግባራት መካከል የ78 ቀን አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የስራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ ወረዳዎች በስራ እድል ፈጠራና በሌማት ትሩፋት ያለባቸውን ክፍተቶች በመለየትና በጥልቀት በመገምገም በቀሪ ጥቂት ቀናት የ90 ቀንን እቅድ ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በስራ እድል ፈጠራና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ በትኩረትና በርብርብ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶአደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ ከተረጂነት ቅነሳ አንፃር የእህል ማከማቻ መጋዘኖችንና የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በማስፋት በ6ቱ ግቦች ላይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
በስራ እድል ፈጠራ እና በሌማት ትሩፋት ክፍለ ከተማውን ሞዴል ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ ይህን እቅድ እውን ለማድረግ በጥራትና በፍጥነት ለመፈፀም የሚያስችል የጋራ መግባባት ሊኖር ይገባል ብለዋል።
የክፍለ ከተማው ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድላየሁ ታምሬ አመራሩ ያሉ ጉድለቶችን ለመሙላት ቁርጠኛ መሆንና በስራ እድል ፈጠራና በሌማት ትሩፋት ተግባራት ወደ ኋላ የቀሩ ተቋማትን በተገቢው ሁኔታ በመገምገምና በመደገፍ እቅዱን ማሳካት ይገባል ብለዋል።
ከምዝገባም ይሁን ከስራ እድል ፈጠራ አኳያ በወጣቶችና በሴቶች ተሳትፎ እንዲሁም በዘርፍ ምጥጥን ላይ ማተኮር እንደሚገባ ጠቅሰው ያሉ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የጥራት መመዘኛ መስፈርቱን የሚያሟላ የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments