አርሶ አደርን ከከተማው ልማት ጋር እያለማች ያለች ከተማ፡ አዲስ አበባ፡፡
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም
የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በከተማ አስተዳደሩ ክልል ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ልማታዊ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ከከተማዋ ልማት ጋር አብረው እንዲለሙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
በባለፉት 7 ዓመታት በተለያዩ የስራ መስኮች ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት ፍላጎት ያላቸው እና የተለዩ አርሶ አደሮች ከ2,470 በላይ መሆናቸውን የአርሶ አደር ልማት ቡድን መሪ ወ/ሮ ደግነሽ በደዊ ገልፀዋል፡፡
ይህ ዕድል ቀደም ብሎ ያልነበረ ከለውጡ ጋር ተያይዞ ለአርሶ አደሮቹ የተመቻቸ ምቹ ሁኔታ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡
ከ190 በላይ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ በኮሚሽኑ በኩል ሁኔታዎች መመቻቸቱን፣ ከ60 በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ፕሮጀክታቸው በሚመለከተው አካል እንዲፀድቅላቸው መደረጉን፤ ከ130 በላይ አርሶ አደሮች ደግሞ በከንቲባ ጽ/ቤት፣ በፕላንና ልማት ቢሮ እና በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው መደረጉን አንስተዋል፡፡
ሌላው ከ55 በላይ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ገብተው የተሻለ ሥራ እየሰሩ ሲሆን ከ35 በላይ የሚሆኑት አርሶ አደሮች ሞዴል መሆናቸውን ወ/ሮ ደግነሽ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ወደ ኢንቨስትመንት ገብተው ከከተማዋ ልማት ጋር አብረው እንዲለሙ በኮሚሽኑ በኩል የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ የመደገፍ፣ ከባንክ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ እና በይዞታቸው ላይ በግል እና ከሌሎች ጋር እንዲያለሙ ግንዛቤ የመስጠት፣ የሙያ ምክር አገልግሎት የመስጠት፣ ፕሮጀክታቸው እንዲጸቅ ከቅንጅታዊ ተቋማት ጋር በጋራ የመስራት እና የመከታተል እንዲሁም የመስክ ክትትልና ድጋፍ በስፋት የተደረገ መሆኑን ቡድን መሪዋ አክለው ገልፀዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments