በ2018/19 ምርት ዘመን የመኸር እርሻ 20,704.78 ቶን ምርት እንደሚገኝ ይገመታል።
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 09 ቀን 2018 ዓ.ም
የ2018/19 ምርት ዘመን የመኸር እርሻ ሥራ በሁሉም ማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ በተቀናጀ መንገድ በክላስተር የዘር ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
የመኸር አዝመራው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተጀመረበት ወቅት የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሀንጋቱ መሀመድ በክፍለ ከተማው የሰብል ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ከተረጂነት ለመውጣት ክፍት መሬቶችን በሙሉ በሰብል መሸፈን እንደሚገባ አሳስበዋል።
አያይዘውም አርሶ አደሮች ወቅቱንና የቀረቡላቸውን ግብዓቶች በአግባቡ በመጠቀም ከቤተሰብ ፍጆታ አልፈው ለገበያ የሚያቀርቡ ምርቶችን ማምረት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ኡርጎ በበኩላቸው ለዘንድሮው የመኸር እርሻ 1,090 ሄክታር መሬት ለሰብል ልማት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
እንደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 2,180 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 226 ኩንታል የተሻሻለ ምርጥ ዘር በማዘጋጀት ከ39,240 ኩንታል በላይ ስንዴ እና ጤፍ ምርት ለመሰብሰብ የታቀደ መሆኑንም አቶ አህመድ አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ከፍተኛ አግሮኖሚስት የሆኑት አቶ ተስፋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው በሁሉም ማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች 7,165 ሄክታር መሬት በመኸር የሚለማ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በከተማ አስተዳደሩ የሰብል ልማት በስፋት ከሚካሄድባቸው ማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
የ2018/19 ምርት ዘመን የመኸር ምርትን በሚፈለገው መጠን ለማግኘት አስፈላጊው የሙያና የግብዓት ድጋፍ ወቅቱን ጠብቆ ለሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተደረገ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።
በዚህም በምርት ዘመኑ (በ2018/19 ምርት ዘመን) የመኸር እርሻ 20,704.78 ቶን ምርት እንደሚገኝ ይገመታል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments