ዜና ትንታኔ
የከተማ ግብርና አብዮት ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ!፡፡
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም አ/አ/ከ/ግ/ል/ኮ
ግብርና — የሰው ልጅ የሰለጠነበት፣ ማህበረሰባዊ እድገቱን የገነባበት እና የህይወቱን ቀጣይነት ያረጋገጠበት ምሰሶ ነው። በዓለም ታሪክ ውስጥ ግብርና ከገጠር ደጃፎች አልፎ ወደ ከተሞች እምብርት መግባት የጀመረው የህዝብ ቁጥር እድገትንና የምግብ ዋስትናን ዘላቂ ለማድረግ በተወሰደ አርቆ አሳቢ እርምጃ ነው።
"ዓለማችን በፈጣን የከተሜነት ማዕበል ውስጥ ትገኛለች። የከተሞች መስፋፋት የሕዝብ ቁጥር መጨመርን፣ የሸማችነትን ስፋትና የምግብ ዋስትና ስጋትን አብሮ ይዞ መጥቷል። ይሁን እንጂ፣ በአህጉራችን አፍሪካ የለውጥ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ፣ ይህንን ፈተና ወደ ትልቅ ዕድል ቀይራዋለች። ከተማ ግብርና አሁን የከተማ ውበትና የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ የውድድር ዘመን ሆኗል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን፣ በኮንክሪት መካከል አዲስ የሕይወት እና የምርት ዘመን ጀምሯል።"
የከተማ ግብርና (Urban Agriculture) በተለይም በቦታ ጥበት ውስጥ የሚከናወነው የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልት ልማት እና ዘመናዊ የአፈር አልባ ቴክኖሎጂ (Hydroponics) የግብርና ስልቶች የብዙ ከተሞች መፍትሄ እየሆኑ መጥተዋል።
በከተሞች የሚታየው ከፍተኛ የቦታ ጥበት ግብርናን ከመሬት ወጥቶ ወደ ጣሪያ ላይ፣ ጓሮ እና ቤት ውስጥ እንዲገባ የቦታ ተግዳሮቶችን እንዲፈታ እድል ፈጥሯል። በመሆኑም ከተማ ላይ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስ፣ ለሸማቹ ትኩስ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
በተለይ ለወጣቶች እና ለሴቶች በቤት ውስጥ የሚከናወኑ አነስተኛ የግብርና ስራዎች የገቢ ምንጭ እየሆኑ ይገኛሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ከተማ ግብርና እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሳይሆን እንደትርፍ ጊዜ ሥራ ብቻ የሚታይበት አመለካከት፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ውስንነት እና በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በጠባብ አካባቢዎች አትክልቶችን እና እንስሳትን ለማርባት ግልጽ የሆነ አሰራር አለመኖር ቀደም ሲል የነበሩ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የታየው ትልቁ ስኬት የአመለካከት ሽግግር ነው! “ግብርና የገጠር ብቻ ነው” የሚለው አመለካከት ተሰብሮ፣ በቤተሰብ ደረጃ በግቢ፣ በጓሮ እና በተቋማት ክፍት ቦታዎች የከተማ ግብርና በስፋት ማበብ ጀመረ።
በ2012 በጀት ዓመት የነበረው 157 ሺህ 502 ተጠቃሚ፣ ዛሬ በፅናትና በትጋት በተሰራው ስራ ወደ 1 ሚሊዮን 283 ሺህ 537 አድጓል!
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments