"ለመጭው አዲስ ዓመት ህገወጥ የእንስሳት እርድና ሥጋ ዝውውርን ለመቆጣጠር በበቂ ሁኔታ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም አ/አ/ከ/ግ/ል/ኮ
ህገወጥ የእንስሳት እርድና ሥጋ ዝውውርን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረሃይል ሥራውን በማዕከል ደረጃ ብቻ ሳይገድብ፣ በክፍለ ከተሞችም ጭምር በማስፋት ግንዛቤ የመስጠት፣ የድጋፍ እና የክትትል ሥራዎችን ማከናወኑ ተገለጸ።
የሰርተፍኬሽን ኢንስፔክሽንና ኳራንታይን ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አስናቀ አወቀ እንደገለጹት ህገወጥ እርድና ዝውውርን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል አጠቃላይ ማስፈጸሚያ እቅድ ተዘጋጅቶ ግብረ-ሃይሉ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ቄራዎች ውስጥ በስታንዳርድ መሠረት አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግ አንጻር ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም መሠረት ከእንስሳት ቅበላ ጀምሮ የቅድመና ድህረ እርድ ምርመራ፣ የላቦራቶሪ እንዲሁም የእርግዝና ምርመራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፤ በቅድመ እርድ ችግር ያለባቸው እንዲወገዱ እና በድህረ እርድ በበሽታ የተጠቃ ካራካስ በጥብቅ ቁጥጥር እንዲወገድና እንዲቃጠል ይደረጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል መጪውን አዲስ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በቄራዎች ድርጅት የሚገኙ የሥጋ ምርመራ ሐኪሞች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የክትትልና ቁጥጥር ባለሙያዎች ቡድን እንዲሰማራ መደረጉ ተብራርቷል። ይህ ቡድን የበዓሉን ሰብአዊና ጤናማ የሥጋ አቅርቦት ደኅንነት በቅርበት በመከተታል ሕብረተሰቡ ጤናማ ምርት እንዲያገኝ ድጋፍ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ህገወጥ የእንስሳት እርድና ሥጋ ዝውውርን ለመከላከል በተዘጋጀው የተቀናጀ ማስፈጸሚያ እቅድ መሠረት ግብረሃይሉ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረወዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments