የወተት ጥራት እና ንጽህናን ለማስጠበቅ የወጡ ዓ...

image description
- In ሰርተፍኬሽን፣ ኢንስፔክሽን፣ኳራንቲንና ሬጉላቶሪ ዘርፍ    0

የወተት ጥራት እና ንጽህናን ለማስጠበቅ የወጡ ዓለም አቀፍ እና ሀገርዊ ህጎች!


ዜና ትንታኔ



የወተት ጥራት እና ንጽህናን ለማስጠበቅ የወጡ ዓለም አቀፍ እና ሀገርዊ ህጎች!
 
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም (አ/አ/ከ/ግ/ል/ኮ)
 
የወተት ጥራት፣ ንጽህና እና ደህንነት የሕዝብ ጤናን ለመጠበቅ ወሳኝ መሠረት በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ፣ በፌዴራል እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ጥብቅ ሕጎችና ደንቦች ተዘጋጅተው በሥራ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሕጎች ከእርባታ ጀምሮ እስከ ፍጆታ ድረስ ያለውን ሂደት ደህንነት ለማስጠበቅ ያለሙ ናቸው።
 
ዓለም አቀፍ ደረጃዎችና ሕጎች
 
በዓለም አቀፍ ደረጃ የወተት ደህንነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የተለያዮ መመሪያዎች እና ህግጋቶች ወጥተው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም፡-
·         ኮዴክስ አሊሜንታሪየስ (Codex Alimentarius): በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እና በምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የተቋቋመው ይህ ድርጅት የወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን የንጽህና አጠባበቅ፣ የኬሚካል ቀሪዎች ገደብ እና ማሸግን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን (Codex Standards for Milk and Milk Products) በማዘጋጀት ተፈፃሚነቱን ይከታተላል፡፡
 
·         የንጽህና መመሪያ (CAC/RCP 57-2004 (የአደጋ ትንተና እና ወሳኝ የመቆጣጠሪያ ነጥቦች) HACCP:- ወተት ከእንስሳት እስከ ሸማች ጠረጴዛ ድረስ በምርት ሰንሰለቱ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ባዮሎጂያዊ፣ ኬሚካላዊ እና ፊዚካላዊ ጉዳዮችን ለመለየትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓለም አቀፍ የደህንነት ሥርዓት ነው።
 
በሀገር አቀፍ (ኢትዮጵያ) ደረጃ ያሉ ሕጎች
 
በኢትዮጵያ የወተት ጥራትና ደህንነትን የመቆጣጠር ኃላፊነት በቅድሚያ የተጠቃሚው ማህበረሰብ ቢሆንም በተቋም ደረጃ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን (FDA)፣ ግብርና ባለስልጣን (AA)፣ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና በከተማችን የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚተገብሩት ነው።
·         የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) አዋጆች: በምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ መሠረት ወተትን ጨምሮ ማንኛውም ምግብ ለገበያ ከመቅረቡ በፊት የደህንነት፣ የንጽህና እና የጥራት ደረጃዎችን ማሟላት እንዳለበት ይደነግጋል። እንደ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በተመሳሳይ እየሰራበት ይገኛል፡፡
 
·         የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት (ESI) ስታንዳርዶች: ጥሬ ወተት ማሟላት የሚገባውን የቅባት መጠን፣ የጥግግት (Density) ልኬት፣ የባክቴሪያ ወሰን እና የንጽህና መስፈርቶች የሚወስኑ የብሔራዊ ደረጃዎች ES ISO 2002 እና ተዛማጅ የጥሬ ወተት ደረጃዎች) አሰራር ተዘርግቷል።
 
·         በከተማችን አዲስ አበባም ወተትን ጨምሮ የግብርና ምርት ጥራት፣ ደህንነትና ንጽህና ለማስጠበቅ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የከተማ አስተዳደሩ አስፈፃሚ አካላትን መልሶ ለማደራጀት ባወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት የተለያዮ አሰራሮችን በመዘርጋት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
 
·         የግብርና ምርት በተለይ የወተት ጥራት፣ ደህንነትና ንጽህና ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች “በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ካንሰርን ጨምሮ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች በጥሬ ወተት ላይ እንደሚጨመር ተረጋገጠ” በሚል እየተራገበ ያለው ዘገባ የተዛባ መሆኑን እንገልጻለን፡፡


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments