"ከሸማችነት ወደ አምራችነት"፡ የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና አዲስ ምዕራፍ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ከሸማችነት አውጥቶ ራሳቸውን እንዲመግቡ ለማስቻል የተጀመረው የከተማ ግብርና ንቅናቄ "ከሸማችነት ወደ አምራችነት" የመሸጋገር ትልቅ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተከናወኑ የተቀናጁ የከተማ ግብርና ሥራዎች ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች የአካባቢያቸውን ፀጋ በመጠቀም ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ ምርት ማቅረብ እንዲችሉ ተደርጓል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡት ዋና ዋና ስኬቶች፦
የግቢና የጓሮ አትክልት ልማት፡ ነዋሪዎች ጓሯቸውን፣ በረንዳቸውን፣ የቤታቸውን ጣሪያና ግድግዳቸውን፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ክፍት ቦታዎችን በመጠቀም ለዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚሆኑ ትኩስ አትክልቶችን ማምረት ችለዋል። አልፎም ለገበያ ተርፈዋል።
የእንስሳት ሃብት ልማት፡ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብና የወተት ላሞች እርባታ፣ ማድለብና የአሣ እርባታ እየተጠናከረ በመምጣቱ የከተማ ግብርና የከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በ2018 በጀት ዓመት ከ615 ሺህ ቶን በላይ ምርት ማምረት የተቻለ ሲሆን በ2019 በጀት ዓመት በ1ኛው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ደግሞ 125, 317 ቶን ምርት ማምረት ተችሏል።
የወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ የሥጋ፣ የእንቁላል፣ የማርና የአሣ ምርት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል።
የገበያ መረጋጋትና የሥራ ዕድል፡ ምርቱ በቀጥታ ለሸማቹ ማኅበረሰብ መቅረብ በመቻሉ ደላሎችን በማስቀረት የኑሮ ውድነቱን አረጋግቷል፤ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶችም ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለው የመዋቅሩ አመራርና ፈፃሚም የተገኘውን ውጤት በእጥፍ ለማሳደግ 7/24 እየሰሩ ሲሆን አጠናክሮ ለማስቀጠልም የጋራ አቋም ይዘው እየሰሩ ይገኛል።
ይህ ስኬት አዲስ አበባ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የከተማውን ነዋሪ ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር እየሰራች ያለው ሥራ ትልቅ ማሳያ ሆኗል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments