
ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ከ40 ዓመታት በኋላ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ
አዲስ አበባ፤ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም
ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ40 አመታት በላይ ተቆጥረዋል። ቫይረሱ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት ከተደረገበት ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ ለብዙ አመታት በከፍተኛ ወረርሽኝ ደረጃ ቆይቷል።
ቫይረሱ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ ዘመቻዎች ሲደረጉ እንደነበር የበርካቶች ትውስታ ነው።
በጊዜው ሲካሄዱ የነበሩት ዘመቻዎች ቫይረሱን ከተጠቂው ያልለየ ነበር። በዘመቻዎችም አስፈሪ ምስሎችን እና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ሲደረጉ የነበረ በመሆኑ በርካታ ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ሰዎች በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲገለሉ እና እንዲፈሩ ያደረገም ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን መድሎ እና መገለል ይቁም የሚል ዘመቻ ሲደረግ እንደነበረ የሚታወቅ ነው፡፡ቫይረሱን በተመለከተም ሰዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዴት መከላከል እንደሚገባቸው የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች በተከታታይ ይሠራ ነበር፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2023 ከ40 ሚልዮን በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ እና ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ የአለም የጤና ድርጅት (WHO) አሳውቋል።
ኢትዮጵያ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭትን የመቆጣጠር እና በ2030 ደግሞ ዜሮ የማድረስ ግብ አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች። በዚህም በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ስርጭቱ በድጋሜ የመስፋፋት አዝማሚያ እያሳየ ይገኛል።
በኢትዮጵያ 8 ሺሕ 257 የሚሆኑ ሰዎች በየአመቱ በኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚያዙ እና 11 ሺሕ 322 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በኤድስ ምክንያት በየአመቱ እንደሚሞቱ በ2015 ዓ.ም የወጣው አገራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ግምት መረጃ ያሳያል።
የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ለመጨመር ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ ለጉዳዩ ተሰጥቶት የነበረው ትኩረት መቀዛቀዝ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
በሀገራችን የኤችአይቪ የስርጭት ምጣኔ 0.87% ሲሆን 605,238 በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤች.አይ.ቪ በደማቸው እንደሚገኝ በወቅታዊ መረጃው ይጠቁማል፡፡
የኤችአይቪ/ኤድስ የስርጭት ምጣኔው ከክልል ክልል የሚለያይ ቢሆንም በከተማ (2.9%) እና በገጠር (0.4%) ልዩነት እንደተስተዋለም አሁናዊ መረጃ ይጠቁማል።
ኤችአይቪ በ1992 ዓ.ም ከነበረበት 3.3% ከፍተኛ የስርጭት መጠን አሁን ወዳለበት 0.87% እንዲቀንስ ከፍተኛ ስራዎች ተሰርተዋል።
ይሁን እንጂ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ምጣኔ በፊት ከነበረው ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር የቀነሰ ቢሆንም በ2030 ምጣኔውን ዜሮ ለማድረስ ከተቀመጠው ግብ አንፃር በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ከፍተኛ ምጣኔ አሁንም በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በዶ/ር ፋሲካ በለጠ እና በአቶ ወንደሰን አካሌ አሰልጣኝነት ለሰራተኞቹ በሁለት ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
እባክዎን እዚህ ይከተሉን!
YouTube ➲ https://bit.ly/4hnxoMs
Telegram ➲ https://bit.ly/4h2cPVT
Facebook ➲ https://bit.ly/4gjsu1M
Tiktok ➲ https://bit.ly/4gdXK2o
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments