
ሁለተኛው ዙር የቦሌ ክፍለ ከተማ የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ መርሃ-ግብር ተካሄደ፡፡
አዲስ አበባ፤ ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም
በዕለቱም ከአንድ ሺ በላይ ለሆኑ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በነፍስ ወከፍ አምስት እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እና አንድ የዶሮ ኬጅ ተሰቷል፡፡
የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ የሌማት ትሩፋት የግብርና ምርት አቅርቦትን በማሳደግ የከተማዋን ነዋሪዎች የምግብ ዋስትና እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በሰብል ምርት፣ በጓሮ አትክልት ልማት እና በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ወገኖች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ፍጆታቸውን ከማሟላት አልፈው የከተማዋ ኢኮኖሚ ማሳደግ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሺፈራው በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ዜጎች ከሸማችነት ወደ አምራችነት ተሸጋግረው የምግብ ዋስትናቸውን እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ አስችሏል ብለዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጆቴ፣ ለተጠቃሚዎች ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ሙያዊ እና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ባዩ ሽጉጤ በሌማት ትሩፋት መነሻነት በተገኘው ስኬት በአሁኑ ወቅት ከተማችን ላይ በቀን ከ18 ሚሊየን በላይ እንቁላል እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰው የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ላደረገው እንቅስቃሴ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments