
የተጠናከረ የአርሶ-አደርና የከተማ ግብርና ልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገለጸ።
-------------------------
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ባደረገው የመስክ ምልከታ አበረታች የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጿል።
ቋሚ ኮሚቴው የኮሚሽኑን የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ያዳመጠ ሲሆን፤ ተግባራዊነቱንም ለማረጋገጥ በከተማዋ እየተሰራ ያለውን የከተማ ግብርና ስራ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው የቡድን አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ባንጉ በሪፖርት የተገለፀው እና በመስክ የተመለከቱት አዲስ አበባ ላይ ከተማ ግብርና በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።
በኮሚሽኑ እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በማስፋፋት ህብረተሰቡ የግብርና ምርቶችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ ጥንካረዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ክፍተቶችን ማስተካከል ላይ ኮሚሽኑ በትኩረት መስራት እንዳለበት የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል።
ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዮ ሽጉጤ ቋሚ ኮሚቴው በዚህ ልክ መስክ ላይ ተገኝቶ ሥራችንን ተመልክቶ ለሰጠን ድጋፍና ግብረ መልስ ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል።
የከተማ ግብርና ዘርፍ ም/ኮሚሽነር አቶ መለስ አንሸቦ ከተማ ግብርናን በዘመናዊ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃብት ለማሰማራት ፌደራል መንግስቱ በተለይም ግብርና ሚኒስትር እና ቋሚ ኮሚቴው ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
የአርሶ አደር ማቋቋምና ልማት ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ ኮሚሽኑ በርካታ ሰው ተኮር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን፣ በቋሚ ኮሚቴው በጥያቄነት የተነሳው ዴኬርን በተመለከተ የተሟላ የዴኬር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
አሁን ያለው የኮሚሽኑ መዋቅር ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት መሸከም ስለማይችል አሁን ላይ የመዋቅር ጥናት ተደርጎ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ አንስተዋል።
ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዮ ሽጉጤ ዛሬ ከተማ ግብርና አበረታች ውጤት እያመጣ ለመሆኑ ማሳያ በቀን ከ2.2 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ለገበያ እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።
አክለውም ክቡር ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ለከተማ ግብርና በሰጡት ልዮ ትኩረት እና በሌማት ንቅናቄ ፕሮግራም አሁን ላይ ከተማ ግብርና አዲስ አበባ ላይ ባህል እየሆነ መምጣት ችሏል ብለዋል።
ሌላው ቋሚ ኮሚቴው የሰጠንን ግብረ መልስ ተቀብለን ተግባራዊ የምናደርግ ይሆናል በማለት ተናግረዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments